Extracted PDF page text
Tesfamicael_Jorjo_paper.doc
Machine-extracted derivative; not a transcript or translation. Reading order, spacing and characters have not been editorially verified. PDF page numbers are file positions, not printed page labels. No OCR has been added.
Open unchanged original PDF · Download unchanged PDF
Extraction status: extracted-unverified.
PDF page 1
View this page in original PDF
1
የምፅዋ ሲምፖዚዩም (ጥር 1974 ዓ/ም)
የተገንጣዮችና የሲ.አይ.ኤ. ግንኙነት
(በተስፋንኪኤል ጆርጆ)
ምንጭ/Source: http://tig.delina.org/tig/qofusenedat/212--1974-
በኤርትራ ክፍለ ሀገር ከዚህ ቀደም የነበረውንና አሁንም በመታየት ላይ ያለውን ነባራዊ ሆኔታ
መሠረት በማድረግ፣ ብዙ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ አገር ደራሲያን፣ የፖለቲካ ተመራማሪዎችና እንዲሁም
ሌሎች በማያዳግም ሆኔታ በፖለቲካ፣ በኤኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች በሰፊው ተንትነውታል፡፡
በመሠረቱ የሁሉም ጸረ-አንድነት ቡድኖች አጀማመር፣ ከገዥ መደቦች ዓላማና ፍላጎት ጋር የተቆራኘ
ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ጸረ-አንድነት ቡድኖች ምንም እንኳ በተለያዩ ስያሜዎች ቢጠሩም፣ በዓላማ
ግን አንድ ናቸው፡፡
ራሱን ጀብሃ ብሎ የሚጠራው ተገንጣይ ቡድን በ1954 ዓ.ም. እነ እድሪስ መሐመድ አደምን በመሳሰሉ
መሳፍንት ከተመሰረተ አንስቶ፣ መሥራቶቹ ለእስልምና ሃይማኖት የምንታገል ዓረቦች ነን በማለት
ፕሮፓጋንዳቸውን ሲያሰራጩ ቆይተዋል፡፡ ይህን መፈክር አንግበውም፣ በጀብሃ ውስጥ የነበሩትን የደጋውን
ሕዝብ ቆሐይን፣ ጽንዓደገል፣ ጋሽና ሠቲት ሀዲዳም በተባሉ ቦታዎች ከህግ ውጭ በሆነ መንገድ ጨፍጭፈዋል፡፡
ንብረቱን ዘርፈዋል፡፡ ይህም በወንበዴው ድርጅት ውስጥ ትልቅ ቅራኔን ፈጠረ፡፡
ይህን በደገኞቹና በቆለኞቹ መካከል የተፈጠረውን ችግር ለማስወገድ፣ ባጋጣሚውም የጀብሃን
አጠቃላይ መዋቅርና ፖሊሲ ለመተለም፣ በ1960 ዓ.ም. አደብሃ (ሳህል አውራጃ) ላይ ስብሰባ ተደርጎ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በስብሰባው ላይ የተላለፉት አስታራቂ ውሳኔዎች፣ በተግባር ሳይተረጎሙ በመቅረታቸው፣
ኢሳያስ አፈወርቂና ተከታዮቹ መገንጠል ጀመሩ፡፡
ነገር ግን እነሱ በሙሉ ክርስትያን በመሆናቸው፣ የጀብሃ ደጋፊ የሆኑት የአረብ አገሮች እርዳታ
ተነፈጋቸው፡፡ ይህም ሆኔታ፣ ከመሪዎቹ የንኡስ ከበርቴ ባህሪ ጋር ተዳምሮ ወደ ኢምፕሪያሊስት ጎራ ጭልጥ
አድርጎ ወሰዳቸው፡፡
ነገር ግን ይህ እነ ኢሳያስ አፈወርቂ ከሃይለስላሴ ፊውዶ ቡርዥዋ መንግሥት ጋር በመመሳጠር፣
የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ለረጅም ጊዜ ሲጨቁን ከቆየው ከአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ጋር የነበራቸው ቀጥተኛ
ግኑኝነትና የጋራ ደባ እስካሁን ለህዝቡ ጆሮ በተብራራ መልክ አልቀረበም፡፡ ስለዚህ ማን ያውራ የነበረ እንዲሉ
በዚያ ወቅት በኢሳያስና በቃኘው የአሜሪካ የጦር ባለስልጣኖች መካከል ይውጠነጠን የነበረውን ሴራ በቅርብ
የማውቀውን ያህል በዚህ ጽሑፍ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
እንደሚታወቀው ከ1946 ዓ.ም. ጀምሮ አሜሪካኖች መረጃዎችን ለመሰብሰብና የሕዝቡን አጠቃላይ
ሳይኮሎጂካል ይዘት ለፍላጎታቸው አመቺ እንዲሆን ለማድረግ በአሥመራ የቃኘው ጣቢያን አቋቋሙ፡፡
እንደዚሁም ከአሥመራ 45 ኪሎ ሜትር ያህል በሚርቀውና ጉራዕ በሚባለው ሥፍራ አንድ የራዳር ጣቢያ
አቋቁመው ነበር፡፡ መረጃ ሊያመጡ የሚፈልጉ ሰዎችንም ለመደለል ይመቻቸው ዘንድ ለአሜሪካኖች ተብሎ
ቀረጥ ሳይከፈልበት ይመጣ የነበረውን ልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጥ በሚሸጡበት (PX) በተባለው ሱቃቸውና (Top Five
Club) በተሰኘው ክበባቸው በተለይ ከፍተኛ ማእርግና ሥልጣን ያላቸውን እያስገቡ ማንኛውንም ዕቃ ሕገ ወጥ
በሆነ መንገድ በርካሽ እየሸጡ እንዲጠቀሙበትና እንዲነግዱበትም ያደርጉ ነበር፡፡ አነስተኛ ደረጃ ካላቸው
ምሁራንና ወጣቶች ጋር ደግሞ ጎልፍ ክበብ በተባለው ማህበራቸውና በወጣቶች ወገኖች ክርስቲያናዊ ማህበር
አማካይነት ሰፋ ያለ ግንኙነት ፈጥረው ነበር፡፡
PDF page 2
View this page in original PDF
2
የገጠሩን ገበሬ እንቅስቃሴ ለመከታተልም ለአደን የሚሔዱ በመምሰልና “በችግኝ ተከላ” ፕሮግራም
አማካይነት በአስተዳደራዊ ጉዳዮችና መስኮች ጣልቃ በመግባት በኢትዮጵያ ባጠቃላይ፣ በተለይም በኤርትራ
ክ/ሀገር ጉዳይ ውስጥ አጥፊ የሆነ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡
አሜሪካኖች በኤርትራ ክፍለ ሀገር የነበረውን ነባራዊ ሆኔታ ለራሳቸው እንደሚስማማቸው አድርገው
በማቀነባበር ሲበዘብዙ የቆዩበት ዘዴ በጣም የረቀቀ ነበር፡፡ እንድያውም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት
እያደገ የሚሄድ የሚሊተሪና የሲቢል ተቃውሞ ስለበዛበት የሚያስተማምን አለመሆኑን የተረዱት ቀደም ብለው
ነበር፡፡
በምትኩም ለረጅም ጊዜ ደጋፊአቸው ሊሆን የሚችል የቡርዥዋ ሥርዓት ለማቋቋም በየአቅጣጫው
ተስማሚ የሆኑ ግለሰቦችንና መሪዎችን በመፈለግ ላይ እንደነበሩ አያጠራጥርም፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ
ባላቸው የፖለቲካ ጥቅም ምክንያት በተለይ ጨለማው መስከረም (Black September) የተሰኘው የፍልስጥኤም
ነጻ አውጭ ድርጅት (P.L.O.) ቡድን በየኤምባሲዎቻቸው የቦምብ ናዳ በማዝነብ ተቃውሞውን ይገልጽ ስለነበር
አሥመራና ጉራዕ የሚገኙትን ጣቢያዎቻቸውን ያጠቃብናል የሚል ስጋት ነበረባቸው፡፡
ሆኔታዎች በዚህ ደረጃ ላይ በነበሩበት ወቅት ነበር፣ እነ ኢሳያስ አፈወርቂ ግኑኝነታቸውን ከአሜሪካኖች
ጋር የጀመሩት፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራን ከ/ሀገር ችግር ለመፍታት
የሚል ሙከራ በማድረግ ላይ ነበር፡፡ እንዲያውም ጥቅምት 7 ቀን 1962 ዓ.ም. በአሥመራ ውስጥ የኤርትራ
ክ/ሀገር መኳንንት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች በተገኙበት የኤርትራ ከ/ሀገር የሰላም ጉባኤ
በሚል ስያሜ አንድ ቋሚ ኮሚቴና ቋሚ ሊቀ መንበር ያለበት ቡድን ተቋቋመ፡፡ ዓላማውም የኤርትራ ክ/ሀገር
ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ በመንግሥትና በተገንጣዮች መካከል የነበረውን የወታደራዊ እንቅስቃሴ ለማቆም
በአመቺ ቦታና ጊዜ ተገናኝቶ ለመነጋገር ነበር፡፡ ይህንንም ምክንያት በማድረግ የዚህ የተጠቀሰው ቀዋሚ ኮሚቴ
ሊቀ መንበር የነበሩት ደጃዝማች ገብረዮሃንስ ተስፋማርያም የፈረሙበት የሰላም ጥሪ ደብዳቤ በዑመር ሐንገለና
በሌሎች አማካይነት ለተገንጣዮች እንዲደርስ ተደረገ፡፡ መልሱም ከተጋድሎ ሐርነት ኤርትራ መ/ጠ/ሐ/ሠ
ኤርትራ ከሜዳ በማለት በ24/11 69 እ.ኤ.አ. የተጻፈ ደብዳቤ “ከልጆቻችሁ ሓሳብ ለሓሳብ ለመለዋወጥ ባስቸኳይ
በፈለጋችሁበት ቀን ክቡርነትዎ በወሰኑት ቦታ በአክብሮት እንጠባበቃለን” የሚል ደብዳቤ አብርሃም ተወልደና
ሰሎሞን ወ/ማርያም በተባሉት ግለሰቦች ተፈርሞ መጣ፡፡
በዚህም መሠረት፣ ከተገንጣይ ቡድን መሪዎች ጋር ለመነጋገርና ለመደራደር፣ በደጃዝማች ገብረኪዳን
ተሰማ (የከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ ዳኛ) ሰብሳቢነት፤ ሌተና ኮሎኔል ገብረእገዚአብሔር መሐረና፣ የኤርትራ
ክፍለ ሀገር ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነርና እኔ ራሴ ተስፋሚካኤል ጆርጆ፣ በአባልነት ያለንበት ኮሚቴ ሕዳር 21
ቀን 1962 ዓ.ም. ተቋቋመ፡፡ እኔ በዚያን ወቅት የደቀመሐረ ወረዳ ገዢ ነበርኩ፡፡ ይህ ኮሚቴ ለመጀመሪያ ጊዜ
ሕዳር 28 ቀን 1962 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ታሕሳስ 5 ቀን 1962 ዓ.ም. ተገንጣዮች ወደሚገኙበት ወደ
ዓላ በረሃ ሄዶ ነበር፡፡ ነገር ግን የተገንጣይ ቡድን መሪዎቹ በኋላቀር አስተሳሰብና በሥልጣን ሽሚያ ምክንያት
በመለያየታቸው በአንድነት ጉዳያቸውን ለማቅረብ አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ኮሚቴው መገናኘትና መነጋገር
የቻለው ከክርስቲያኑ ተገንጣይ ቡድን ጋር ብቻ ነበር፡፡ ከኮሚቴው ጋር ቀርበው የተነጋገሩት የቡድኑ ቀንደኛ
መሪዎችም፣ አብርሃም ተወልደ፣ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ሰለሞን ወ/ማርያም፣ ሀብተስላሴ ገ/መድህን፣ ወ/ሚካኤል
ሃይለ፣ በራኺ ንጉሠና ሌሎችም ነበሩ፡፡
ያቀረቡትም ሐሳብ “እኛ ከእስላሞች ተለያይተናልና… እነሱን መውጋት እንድንችል ከመንግሥት
ማተሪያላዊና ሞራላዊ እርዳታ ይሰጠን” የሚል ነበር፡፡ ኮሚቴውም መንግሥት በዜጎቹ መካከል የሃይማኖት
ልዩነት እንደማይፈጥርና ጥያቄአቸውም ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ በበኩላቸው እጃቸውን ለመስጠት
ዝግጁ ከሆኑ ግን መንግሥት እንደሚቀበላቸው ገለጸላቸው፡፡ ይህም በወንጀል መዝገብ ቁ. 557/62 መከላከያ
ምስክር ሌ/ኮሎኔል ገብረእግዚአብሔር መሐረና በሚለው በገጽ 27 ላይ ሰፍረዋል፡፡
ተገንጣዮቹም፣ “ቁጥራችን ከፍተኛ ስለሆነ ተሰባስበንና ተመካክረን እጃችንን እስከምንሰጥ የቀሩት
እንደኛ የመሰሉት ወንድሞቻችን አደጋ ላይ እንዳይወድቁ የተነጋገርንባቸው ጉዳዮች ይዘትና የመገናኘቱም
ጉዳይ በከፍተኛ ምስጢር እንዲጠበቅልን” ስላሉና ይህም ሀሳባቸው ተቀባይነት ስላገኘ የሚሰበሰቡበት ቦታና ጊዜ
ተወሰነ፡፡ ይሄም በወንጀል መዝገብ ቁ. 557/62 በደጃዝማች ተስፋዮሐንስ በርሄ ም/እንደራሴ የቀረበ የመካላከል
ምስክር በሚለው ገጽ 63 ላይ ሰፍረዋል፡፡ ኮሚቴው ይህንን ሁሉ እንደተለመደው ለመንግሥት አቀረበ፡፡ ነገር
ግን በምስጢር ይጠበቅልን ብለው ቃል ያስገቡን ጉዳይ ሊከበርላቸው አልቻለም፡፡ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ
በአሜሪካና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ምሥጢራዊ መረጃዎችን በመለዋወጥ በኩል (Exchange of
Confidential Information) የነበረው ስምምነት ጠንካራ በመሆኑ ኮሚቴው በምስጢር ያቀረበው ሪፖርት ሁሉ PDF page 3
View this page in original PDF
3
አሜሪካኖቹ እጅ ወደቀ፡፡ እነሱም (አሜሪካኖች) በበኩላቸው ከዚያ በኋላ “ሰልፊ ነጻነት” በሚል ስያሜ ተቋቋሞ
የነበረውን የኢሳያስ ቡድን ለመገናኘት ለብቻቸው ሩጫ ጀመሩ፡፡
በዚህ ዓይነት አሜሪካኖቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊገናኙና ሊነጋገሩ የቻሉት ሀብተሥላሴ ገ/መድህን
ከተባለውና “ከሰልፊ ነጻነት” ተገንጣይ ቡድን መሪዎች መካከል አንደኛው ከነበረው ግለሰብ ጋር ነበር፤
ንግግሩም የተደረገው እኔ ራሴ በተገኘሁበት በቃኘው ጣቢያ ግቢ ውስጥ ሪቻርድ ኮፕላንድ ከሚባለው “የችግኝ
ተከላ ፕሮጀክት” በሚል ሽፋን ከብዙ ሰዎች ጋር እየተገናኘ ስለላ በሰፊው ያካሄድ ከነበረው አሜሪካዊ ጋር
ነበር፡፡
ሪቻርድ ኮፕላንድ ከሀብተሥላሴ ጋር ባደረገው የሀሳብ ልውውጥ ተገንጣይ ቡድኖቹ በአሜሪካኖች ላይ
የቱን ያህል ከፍ ያለ ጥላቻና ቅያሜ እንደነበራቸው መረዳት ቻለ፡፡ አድሃሪውን የሃይለስላሴ መንግሥት አቅፈው
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይ በኤርትራ ክፍለ ሀገር ሕዝብ ላይ ያደርሱ የነበረውን ጭቆና በመዘርዘር
የቱን ያህል እንዳስቆጣቸው ሀብተስላሴ በግልጽ አስረዳው፡፡ ኮፕላንድ፣ ይህ ሆኔታ አሜሪካኖቹ ከመጀመሪያ
ጀምሮ ይፈሩት የነበረውን ቅዋሜና፣ ወታደራዊ ጥቃት በቃኘውና በጉራዕ ጣቢያዎቻቸው ላይ፣ ወደፊትም በቀይ
ባህርና በአፍሪካ ቀንድ ባላቸው የረጅም ጊዜ ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ ክስረት ሊያደርሱ የሚችሉ መሆናቸውን
ለመረዳት ቻለ፡፡ ስለሆነም ከተገንጣይ ቡድኖች ዋና ዋና መሪዎች ጋር እንዲያገናኘውና የጋራ ስምምነት
ለመቀየስ እንዲቻል ያደርግ ዘንድ ሀብተሥላሴን ጠየቀ፡፡ ከዚህ ውይይት በኋላ ሀብተሥላሴ ከቃኘው ጣቢያ
ጓደኞቹ ወደነበሩበት ወደ ዓላ በረሃ ተመልሶ ሄደ፡፡
ሃብተሥሳሌም “የሰልፊ ነጻነት” የበላይ መሪዎች ከነበሩት ከአብርሃ ተወልደና ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር
ስለ ጉዳዩ ከተወያየበት በኋላ ወደ ደቀምሐረ ከተማ ተመልሶ አሜሪካኖቹ ከዋና ዋናዎቹ የሠልፊ ነጻነት
መሪዎች ጋር ሊነጋገሩ የሚችሉበትን አጀንዳ እንዲያዘጋጅ ታዘዘ፡፡ ከአሜሪካኖቹ ጋርም የግንኙነት ቀጠሮ
አደረገ፡፡ በቀጠሮው መሠረትም ሪቻርድ ኮፕላንድ ደቀምሐረ ሲመጣ ጓደኛው የነበረውን ሪቻርድ ሲወልንና
አንድ ትልቅ የጦር መሣሪያ ካታሎግ ይዞ መጣ፡፡
በወቅቱ በተደረገው ውይይት አሜሪካኖቹ በመጀመሪያ ደረጃ ለማወቅ የፈለጉት ተገንጣዮቹ የጦር
መሣሪያ የሚያገኙበትን ምንጭና የንቅናቄአቸውን የውጭ ደጋፊ ሃይላት ነበር፡፡
ሀብተሥላሴንም በመጀመሪያ የጠየቁት ምን ዓይነት ጠመንጃና ሌላ መሣሪያ እንዳላቸው ነበር፡፡ እሱ
ደቀምሐረ ይዞት መጥቶ የነበረውንም ክላሽን-ኮቭ አውቶማቲክ መሣሪያ ተውሰው፣ ቃኘው ጣቢያ ከወሰዱ በኋላ
ፎቶግራፍ አንስተውና መርምረው መለሱለት፡፡ አሜሪካውያኑ በተጨማሪም የተገንጣይ ቡድኑ ዋና ዋና መሪዎች
ስለቡድናቸው አጠቃላይ ፖሊሲ፣ ከጀብሃ ጋር ስላላቸው ቅራኔ፣ ለጀብሃ ሶሻሊስት አገሮች በፍልስጥኤም ነፃ
አውጪ ድርጅት በኩል በእጅ አዙር እርዳታ እንደሚሰጡና “ ሰልፊ ነጻነት” ከአሜሪካ ጋር ለማድረግ
የሚፈልገውን ግንኙነት የሚገልጽ ኦፊሴላዊ ደብዳቤ በጊዜው የቃኘው ጣቢያ አዛዥ ለነበረው፣ ኮሎኔል ማሙዘር
እንዲጽፉ ያደርግ ዘንድ ሀብተሥላሴን ጠየቁት፡፡ በዚህ መሠረት ደብዳቤው በመሪዎቹ ተረቅቆና ተዘጋጅቶ
በፖስታ ቤት እንዲላክ ተደረገ፡፡
በደብዳቤው ውስጥ የሰፈሩት ዋና ዋና ነጥቦችም፤
1ኛ/ በዓላ በረሃ የሚገኙት ታጋዮች፣ ክርስቲያን በመሆናቸው ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካና የመሣሪያ
ርዳታ ከዓረብ መንግሥትና፣ ከሶሻሊስት አገሮች በእጅ አዙር በሚያገኘው የጀብሐ ቡድን በየቀኑ የሚገደሉና
የሚታረዱ መሆናቸውን፤
2ኛ/ ጀብሃ የያዘችው ፖለቲካ ጭልጥ ያለ የሃይማኖት ይዘት ያለውና የእስራኤልና የአሜሪካ ዓይነተኛ
ጠላት ከሆኑት የአረብ ሀገሮች ጋር ፖሊሲው የተዛመደ መሆኑን፤
የሰልፊ ነጻነት ቡድን ዋና ዓላማ ግን “ተራማጅና ዲሞክራቲክ እንቅስቃሴ” ለማካሄድ መሆኑን
የሚገልጽና አሜሪካም የሚያስፈልገውን እርዳታ እንድትሰጣቸው የሚማፀን ነበር፡፡
(ይህ ደብዳቤ በ21/9/62 ቁ. 1039/18/31 ማህደር ቁ. ሀ/1/19ሠ2 በእንግሊዝኛ ጽሑፍ ሰፍሮ ይገኛል፡፡)
በዚሁ ወቅት ይኸው ተገንጣይ ቡድን ተመሳሳይ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ቆንስልም [በአስመራ የአሜሪካ
ቆንስላ ጽ/ቤት መሆኑ ነው] ጽፎ ነበር፡፡ የደብዳቤውም ዋና ይዘት ባጭሩ፣ “ኮሚኒስቶች እስላሞችን ስለሚረዱ
እናንተ ምዕራባዊያን ደግሞ እኛን ልትረዱ ይገባል” የሚል ነበር፡፡ ይህ ደብዳቤ የተጻፈው እንደ አውሮጳ
አቆጣጠር በ5/4/1970 ሲሆን፣ ቆንስላው ደብዳቤውን የኤርትራ ከ/ሀገር ምክትል እንደራሴ ለነበሩት
ለደጀ/ተስፋዮሐንስ በርሄ ሚያዝያ 1/62 ዓ/ም. አስረክበዋል፡፡ ይህም በመዝገብ ቁ/ሀ/1/1042 ደብዳቤ ቁጥር
1091/18/31 ሰኔ 4 ቀን 1962 ዓ/ም. ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም መንግሥቱ ባይሩ ዑቅቢት በተባለው
ግለሰብ አማካይነት፣ ከሌላ ካልታወቀ የውጭ አገር ሃይል ተመሳሳይ ዕርዳታ ለነ አብርሃ ተወልደና ለነ ኢሳያስ PDF page 4
View this page in original PDF
4
አፈወርቂ የሚገኝበት መንገድ ተቀይሶ እንደነበረና ከተባሉትም የውጭ ሀገር ሰዎች ጋር አገናኝቷቸው እንደ
ነበረ ሃብተሥላሴ ገብረመድህን ተማርኮ በነበረበት ጊዜ በሰጠው ቃል አረጋግጡዋል፡፡ ይኸም በመዝገብ ቁ.
ሀ/1/1042 ደብዳቤ ቁ. 1091/18/31 አሥመራ ሰኔ 4/62 ዓ.ም ተጠቅሶአል፡፡
አሜሪካኖቹም፣ በበኩላቸው የመጣላቸውን ደብዳቤ በደስታ ተቀበሉት፡፡ ከዚያም በኋላ የቡድኑ መሪ
የሆነው ኢሳያስ አፈወርቂ ራሱ መጥቶ ከአሜሪካኖቹ ጋር እንዲነጋገር ቀጠሮ ተደረገ፡፡ በተባለውም ቀን እኔ
ራሴ በማሽከረክረው የመንግሥት ላንድሮቨር መኪና ከደቀምሐረ ዓላ በረሃ ድረስ ሔጄ፣ ኢሳያስን ወደ አሥመራ
ይዠው መጣሁ፡፡ በአሥመራ ከተማ ውስጥም፣ ለሁለት ሰዓት ያህል በመኪናው ሳንሸራሽረው ቆይቼ በቀጠሮው
ሰዓት ቃኘው ጣቢያ ወሰድሁት፡፡ አሜሪካኖቹም የሴኩሪቲ ችግር እንዳይፈጠር ብለው ውይይቱ ሚስተር
ቦውሊንግ በተባለው የቃኘው ጣቢያ ሴንትራል ኢንተሊጀንስ ዲፓርትመንት ባልደረባ መኖሪያ ቤት፣ ማለትም
ቅዱስ ፍራንሲስኮ ካቴድራል አጠገብ ተካሄደ፡፡ በአሜሪካኖቹ በኩል ከሪቻርድ ኮፕሊንግ ጋር ሌሎች ሶስት
የሚሆኑ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ነበሩ፡፡
በንግግሩ ወቅት ኢሳያስ ካነሳቸው ነጥቦች መካከል፤
1/ የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመመሳጠር የኤርትራን ዕድል በመወሰን ጉዳይ
የሰፊውን የኤርትራ ሕዝብ ፍላጎት የማያሟላ የፌደሬሽን አቋም በመፍቀድዋ፤
2/ ፌደራላዊ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ ደግሞ የኤርትራን ሕዝብ ለማጥፋትና እንቅስቃሴውን
ለመደምሰስ ስፍር ቁጥር የሌለው መሣሪያና አማካሪዎች ለኢትዮጵያ መንግሥት ማቅረቡዋ በነሱ ዘንድ የተወገዘ
ድርጊት መሆኑን፤
3/ የዓረብ አገሮች ጀብሃን በመርዳት ቀይ ባህርን የዓረብ ግዛት ለማድረግ መወሰናቸውንና “ተራማጅ
ድርጅትና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት” ለመመስረት በሚደረገው ትግል ያለፈውን ድርጊታቸውን በማረምና
በማስተካከል የሱን ቡድን እንዲተባበሩ ሙሉ እርዳታን የሚጠይቁ ይገኙባቸዋል፡፡ አሜሪካዊያኑም ከኢትዮጵያ
መንግሥት ጋር በዓላ በረሃ ይደረግ የነበረውን ድርድርና የጀብሃንም አኳኋን በሚገባ ስለሚያውቁ “ጀግኖቹ
እንደተሰቃያችሁና እንደተገደላችሁ በይፋ የምናውቀው ነገር ነው፡፡ ከነሱ መገንጠላችሁም የሚደገፍ ነው” ካሉ
በኋላ የፍልስጥኤም ቡድን አካል የሆነው “ጨለማው መስከረም” (Black September) ኤምባሲዎቻችንን
በመደብደብ በየቦታው በገንዘብ በተገዙ የአገር ሰዎች ስለሚጠቀም፣ የዚህ ድርጅት መሣሪያ እንዳትሆኑ፤
በበኩላችሁ በንብረታችንና በአባሎቻችን ላይ ጉዳት እንዳታደርሱና፣ ለመከላከልም ቃል ከገባችሁልን አንዳንድ
የማቴሪያል እርዳታ እናቀርባለን በማለት ነው የጠራናችሁ” ብለው አስረዱ፡፡ ኢሳያስም የእርዳታው ጉዳይ
በዓላው ቡድን በኩል ተቀባይነት እንዳለው ገልጾ ጨለማው መስከረም (Black September) የተባለው ቡድን
ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት መከላከል ግን ከቡድኑ (ተገንጣይ) አቅም በላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡
አሜሪካዊያኑም ንግግራቸውን በመቀጠል “በታሪክ፣ ኤርትራ በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በደማዊ
መተሳሰር ከኢትዮጵያ ሳትነጠል ቆይታለች፡፡ በኤርትራ ውስጥ የውስጥና የውጭ ቅራኔ ሳቢያ በጉዳዩ ጣልቃ
ገብተን ሆኔታውን ለማረጋጋት በኤርትራ የፌደረሽን አቋም ወሰድን፡፡ አሁን ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው
ስርዓት በመዳከም ላይ ስለሚገኝና፣ የሚተካውም የተደራጀ ፓርቲ ባለመኖሩ፣ እንደሌሎቹ የአፍሪካ ሀገሮች ሁሉ
ወታደራዊ አስተዳደር ይመጣል ብለን እንፈራለን፤ እምነትም የለንም” በማለት፤
ሀ/ የቃኘው ጣቢያ ህልውና እንዲጠበቅና ሌላ ተመሳሳይ ጣቢያም በቀይ ባሕር አካባቢ እንዲቋቋም
ከሚተባበር ፤
ለ/ ፀረ ሶሻሊስት የሆነ አቋም ከሚይዝና የሶሻሊዝምን መስፋፋት ከሚቃወም፤
ሐ/ ለአንድ ዴሞክራሲያዊት የኤርትራ መንግሥት የሚታገል ቡድን ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነን”
በማለት አስረዱት፡፡
በጊዜው የኤርትራ ክ/ሀገር እንደራሴ የነበረው ራስ አሥራተ ካሣ “ለሰልፊ ነፃነት” ሶስት አማራጭ
ሰጥቷቸው ነበር፦ እነሱም፤
1ኛ/ ሁሉም በምህረት ገብተው በየፊናቸው ትምህርትም ሆነ ሥራ እንዲቀጥሉ፤
2ኛ/ ከጀብሃ ጋር መለያየታቸውን በይፋ ለማሳወቅ ጀብሃን በጦር ሃይል ወግተው መጣላታቸውን
በግልጽ እንዲያረጋግጡ፤ ይህን ካደረጉ የመሣሪያ እርዳታም ሊሰጣቸው እንደሚችል፤
3ኛ/ ሁሉም በምህረት ገብተው ወታደራዊ ትምህርት በመቀበል በጀብሃ ላይ ያላቸውን ቂም በቀል
ከጦሩ ጋር በመተባበር እንዲወጡ፤ የሚሉ ስለነበሩ፣ አሜሪካኖቹም እነዚህን አማራጮች መነሻ በማድረግ
ለኢሳያስ ምክራቸውን ለገሱት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ጀብሃንና የኢትዮጵያን መንግሥት ጦር ባንድነት ለመቋቋም
አቅም እንደሌለው ገለጡለት፡፡ ስለሆነም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የመጀመሪያውን ድርድር፣ በከፊልም
ቢሆን፣ እንዲቀጥልበት መከሩት፡፡ ለዚህ የሚሻለው ዘዴ ከቡድኑ መሪዎች መካከል ጥቂቶቹ በምህረት ገብተው
የቀሩት በኢሳያስ መሪነት በበረሃ ጸረ ጀብሃ ትግሉን እንዲቀጥሉ ማድረግ፤ መሆኑን በዝርዝር አስረዱት፡፡ ይህን
ማድረግ ከቻለ አሜሪካኖቹ ከአሥራተ ካሣ ጋር በመስማማት የኤርትራ ክ/ሀገር ተወላጆች ብቻ የሚገኙበት PDF page 5
View this page in original PDF
5
ጠንካራ የኮማንዶ ሃይል አሰልጥነው እንደሚልኩለትና ጀብሃን በተጨማሪ ሃይል እንደሚመልሱለት ቃል
ገቡለት፡፡
ሆኔታውን ለማቀላጠፍ፣ የጀብሃንም አቅም በተሎ ለማዳከምና የምታገኘውም እርዳታ እንዲቋረጥባት
በአረቦችና በእስራኤል መካከል ያለውን የመካከለኛውን ምስራቅ ጦርነት በማቀጣጠልና ጊዚያዊ ጦርነት
በመክፈት የአረብ አገሮች በአካባቢያቸው ብቻ እንዲወሰኑ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገለጡለት፡፡ በዚህም ጊዜ
በኢትዮጵያ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶ የፖለቲካ ሥልጣኑን የሚጨብጠው አካል ኤርትራን በፌደራላዊ
መንግሥት የሚያውቅ ይሆናል፡፡ አሜሪካም ከዚሁ ክርስቲያናዊ መንግሥት ጋር ይተቃቀፋል፡፡ ምክንያቱም
የቀይ ባህር ጌትነት ያመለጣቸው የዓረብ አገሮች የተዳከመውን ጀብሃ መርዳት ብቻ ሳይሆን በወታደራዊ
ሃይልም ለመግባት ሳይሞክሩ ስለማይቀሩና “ሰልፊ ነፃነት” ብቻውን ሊቋቋማቸው ስለማይችል ነው በማለት
አስረዱት፡፡ ኢሳያስ ግን “የኤርትራ ነፃነት ምንም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ስለሆነ፣ ፌደረሽን የሚባል ነገር
አልቀበልም” አለ፡፡ አሜሪካዊያኑም በበኩላቸው “የኤርትራ ጥያቄ የውጭ ጥያቄ እንጂ የውስጥ ጥያቄ አለመሆኑን
የሚያረጋግጡ አንዳንድ ነጥቦች ስለሚኖሩ የጠቀስንላችሁን ሦስት ዓላማዎች ለማሟላት ከተስማማችሁ ሙሉውን
ነፃነታችሁን የምንደግፍ መሆናችንን እንገልጻለን” በማለት “በናንተውና በምንልከው የኮማንዶ ኃይል ብርታት
የጀብሃ ድክመት ከታየ በኋላ በኢትዮጵያ የሚቋቋመው አዲሱ መንግሥት ኤርትራን በፌደራላዊ ስርዓት
በሚያውቅበት ጊዜ እናንተ አትቀበሉ፡፡ በዚሁ ጊዜ እነኛ አስቀድመው ምህረት ጠይቀው የገቡት ጓደኞቻችሁ
እኛ በምናቀርብላቸው የመሣሪያና የወታደራዊ ስልት እውቀት ደልበው ስለሚጠብቁ በብዛት ወደ እናንተው
ይጎርፋሉ፡፡
“ከደጋው ክፍል ወደ ቆላው በመውረድ ደግሞ የባህር ጠረፎችን በቁጥጥራችሁ ሥር ስለምታደርጉ
በቪየትናሙ ጦርነት ከቪየት ኮንግ የማረክነውን የሩሲያ መሣሪያ በሙሉ በመርከብ እናቀርብላችኋለን፡፡”
“አሜሪካ ሠራሽ መሣሪያዎችና ቁሳቁሶች ግን በሶስተኛው ዓለም የተያያዝነውን ፕሮፓጋንዳ
ሊያቀዘቅዝብን ስለሚችል አናቀርብላችሁም፡፡ ጉዳዩ እንዲፋጠንም በኢትዮጵያ የሚመሠረተው አዲስ
መንግሥት የምታውጁትን መንግሥት በይፋ እስከሚያውቀውና እስከሚቀበለው ድረስ የምንሰጠውን ማተሪያላዊና
ሌላም እርዳታ በመጠኑ በማቋረጥ ተጽእኖ እናደርግበታለን” አሉ፡፡
ኢሳያስም ይህን ፕላን በቲዮሪ ደረጃ ከሰማ በኋላ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን ምን ዋስትና አለው?
በማለት ጠየቀ፡፡ አሜሪካኖቹም “ፖለቲካ የቁማር ጨዋታ ስለሆነ ቁማር ተጫወት” እናንተ የምትፈልጉት ነጻነት
ነው፡፡ እኛ ደግሞ የምንሻው የቀይ ባህር ይዞታችን እንዲጠናከር ስለሆነ፣ ይኸው ዋስትናችን ነው” ብለው
መለሱለት፡፡
ይህን አጠቃላይ ውይይት ካደረጉ በኋላ አሜሪካኖቹ ስለ ኤርትራና ስለ ኢትዮጵያ የወደፊት ህልውና
ቀደም አርገው የዚህ ዓይነት የተራቀቀ ፖሊሲ ማውጣታቸው ያስደነቀው መሆኑን ኢሳያስ ገለጠላቸው፡፡
ስለተለዋወጥዋቸው ሀሳቦች ግን በሰፊው ከበረሃ ጓደኞቹ ጋር ተወያይቶ የመጨረሻውን መልስ በተከታታይ
እንደሚልክላቸው አስታውቆ ስብሰባው አበቃ፡፡ እኛም ለአዳርና ለግብዣ ተመልሰን በቃኘው ጣቢያ በተለይ
ተዘጋጅቶልን ወደነበረው የሚስተር ኮፕላንድ መኖሪያ ቤት ሔድን፡፡
በማግሥቱ ኢሳያስን ወደ በረሃ ለመመለስ አሜሪካኖቹ ብዙ ዝግጅት ማድረግ አስፈለጋቸው፡፡
ምክንያቱም በዚያን ወቅት በአሥመራ መውጫና መግቢያ በሮች ሁሉ የተሰማሩት ፀጥታ አስከባሪዎች ከባድ
ፍተሻ ያካሔዱ ስለነበር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነበር፡፡ ስለሆነም ኮፕላንድ ራሱ ሾፌር ሆኖ
የአሜሪካን ባንዴራ የሚውለበለብበትና፣ የዲፕሎማቲክ ታርጋ ያለውን እንዲሁም የሗላው መስተዋት በመጋረጃ
የተሸፈነ ካዲላክ መኪና በማዘጋጀት እኔንና ኢሳያስን ይዞ በምፅዋ መንገድ በኩል የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪ
ወታደሮችን ሰላምታ እየተቀበልን ወደ ነፋሲት አመራን፡፡ ከነፋሲት ወደ ደቀምሐረ በሚወስደው መንገድ
እስከማይሐባር አካባቢ ድረስ ኢሳያስን ይዘነው ሔድንና እዚያ ይጠብቁት ለነበሩት ጓደኞቹ አስረክበነው፣ እኛ
ደግሞ በደቀምሐረ በኩል ዞረን ወደ አሥመራ ተመለስን፡፡
አሜሪካኖቹ ወዲያውኑ ይህን ስምምነት ተግባራዊ የሚያደርጉበትን ዝግጅት ተያያዙት፡፡ ጨለማው
መስከረም የተባለው የፍልስጥኤም ነጻ አውጭ ድርጅት ጥቃት ያደርስብናል በሚል ሽፋን ራስ አሥራተ ካሣን
በማግባባት ከሀገራቸውና፣ በፀጥታ አስከባሪዎች ከየቦታው ተቀብረው የተገኙትን፣ እንደዚሁም በጦርነት
የተማረኩትን አያሌ መሣሪያዎች በኤንትረ ከባድ መኪናዎች አስጭነውና ሸፋፍነው በማሰራጨት ከኤርትራ
እስከ መሀል አገር ያሉት የአሜሪካ ደጋፊዎች በየቦታው እንዲጠናከሩ አደረጉ፡፡ ወዲያውኑ በምስራቃዊና
በምዕራባዊ የኤርትራ ቆላዎች ከበድ ያለ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለማካሄድ ከመሃል አገር ቁጥሩ በርከት ያለ
ሠራዊት እንዲመጣ ተደረገ፡፡ ምክንያቱም በኤርትራ ክ/ሀገር ውስጥ ጦርነት ማቀጣጠል አንድ ስንኩል
መንግሥት በማሃል ኢትዮጵያ ለመፍጠር ለታቀደው መፈንቅለ መንግሥት የመጀመሪያው ቅድመ ሆኔታ
እንዲሆን ታቅዶ ነበር፡፡ PDF page 6
View this page in original PDF
6
ይህ በእዚህ እንዳለ እነዚያ በቃኘው ጣቢያ ከሃብተስላሴ ገብረመድህንና ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር
የተካሄዱት ስብሰባዎች በድብቅ በቴፕና በፎቶግራፎች ተቀርጸው ስለነበር የካቲት 17 ቀን 1962 ዓ.ም. ፍሬ
ነገሩ በጽሑፍ ሰፍሮ ከነፎቶግራፎቹ በአሥራተ ካሣ የአሥመራ ሰላይ በነበረው በሚስተር ግለንቦየት በተባለ
አሜሪካዊ ተደርሶበት ለአሥራተ ካሣ ቀረበ፡፡ ለዚሁም ወንጀል መዝገብ ቁጥር 557/62 ቀኛ/ ካሳሁን መከላከያ
ምስክር ገጽ 28 የሚለውን መመልከት ይቻላል፡፡
በዚህ ምክንያት እኔም ከደቀምሐረ ባስቸኳይ ተጠርቸ ተጠየቅሁ፡፡ ራስ አሥራተ ካሣም ኢሳያስ
አፈወርቅና ጓደኞቹ ከአሜሪካኖቹ ጋር ለመገናኘታቸው እኔን በሃላፊነት ለመጠየቅ ሞከረ፡፡ እኔ ግን በበኩሌ
አሜሪካኖቹ እንደልባቸው በየገጠሩ ሁሉ እንዲዘዋወሩ በመንግሥት ስለተፈቀደላቸው ሰፊ ግንኙነት
ማቋቋማቸውን ገልጨ፣ ጉዳዩ የኔ ሃላፊነት አለመሆኑን አስረዳሁ፡፡ እንደዚሁም እኔ የወረዳው ገዢ በመሆኔ ብቻ
ሳይሆን፣ መንግሥት የሰላም ጉባኤ በማለት ያቋቋመው ኮሚቴ ተወካይም ስለሆንኩ፣ በዓላ በረሃ የሚካሄደውን
እንቅስቃሴ በቀጥታ ለመከታተል ኃላፊነት እንደነበረብኝ በተጨማሪ አስረዳሁ፡፡ ይህንን ከገለጽኩ በኋላ
ሆኔታውን ወደፊት በምስጢር እየተከታተልኩ ዕለት በዕለት ሪፖርት እንዳቀርብ በአሥራተ ካሣ ትእዛዝ
ተሰጠኝ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን የአሥራተ ካሣ የወደፊት ሴራ በየአቅጣጫው መወራት በመጀመሩ
የተፈጠረውን ውዥንብር ለማርገብ እኔ እንድታሰርና በወንጀል እንድከሰስ ተደረገ፡፡
ራስ አሥራተ ካሣም ስሙን ለመጠበቅ ሲል በምስጢር ይደራደራቸው የነበሩት የዓላ በረሃ ተገንጣይ
ቡድን አባሎች በጦር ኃይል እንዲመለሱ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ምንም እንኳ ከ1963 ዓ.ም. ወዲህ በቀጥታ ያልተሳተፍኩባቸው ቢሆንም፣ አንዳንድ
የተገንጣይ ቡድኑ አባሎች በነገሩኝና እኔም ባደረግሁት ክትትል ላይ በመመሥረት በሻዕቢያ ውስጥ የታዩትን
ጉልህ ሆኔታዎች ቀጥሎ ባጭሩ ለመጥቀስ እሞክራለሁ፡፡
- በኤርትራ ክ/ሀገር ውስጥ ከ1962-1964 ዓ.ም. ድረስ ጀብሃ፣ ዑብል፣ ሕዝባዊ ኃይልና ሰልፊ ነጻነት
የሚባሉ አራት ድርጅቶች ነበሩ፡፡ ጀብሃ በ1964 ዓ.ም. የመጀመሪያውን ጉባኤ ባደረገችበት ወቅት ሌሎቹ ሶስቱ
ቡድኖች በጉባኤው ላይ ያልተገኙ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ መመሪያዎችንም ባለመቀበላቸው በጦርነት
ልታጠፋቸው ወሰነች፡፡ እነዚህ ሶስት ቡድኖችም እርስ በርስ ከመቃቃር ይልቅ በአንድ ግንባር ሥር ተሰልፈው
ጀብሃን እንዲቋቋሙ ያስገደድዋቸው ብዙ ሆኔታዎች ነበሩ፡፡
- ሕዝባዊ ኃይል ውስጥ የነበሩት የዑስማን ሳልሕ ሳበ ወገኖች የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች
በመሆናቸው ከአረብ አገሮች በቂ ገንዘብና መሳሪያ አገኙ፡፡ የወቅቱ ደካማ ጎናቸው ግን በቂ የሰው ሃይል ማጣት
ነበር፡፡ በጊዜው ብቁና ብዙ የሰው ሃይል ያከማቸው በኢሳያስ የሚመራው “የሰልፊ ነጻነት” ቡድን ነበር፡፡
ዑስማን ሳልህ ሳበም ከውጭ “በእርዳታ” ለሚያገኘው መሣርያ ሠራዊት ስላስፈለገው፣ ከሰው ሃይል በስተቀር በቂ
ድርጅትና መሣሪያ ያልነበረው ኢሳያስና ያለ ሠራዊት በርካታ መሣሪያዎችን ያካበተው ሳልህ ሳበ ሁለቱም
ለየጥቅማቸው ሲሉ ለመቀራረብ ወሰኑ፡፡
- ጀብሃ በ1964 ዓ.ም. የሕዝባዊ ኃይልንና የዑብል ቡድን አባሎችን ለመደምሰስ ማጥቃት ስለጀመረች
የሁለቱ ቡድኖች አባላት ከሳሕል ሸሽተው ወደ ሱዳን ገቡ፤ በዚህ ወቅት በሣህል በረሃ ውስጥ የቀረው በኢሳያስ
የሚመራው የሰልፊ ነጻነት ቡድን ብቻ ስለነበር የዑብል፣ የሻዕቢያና የሰልፊ ነጻነት ቡድን መሪዎች የጀብሃን
ጥቃት ለመቋቋም ቤይሩት ላይ በ1965 ዓ.ም. ተሰብስበው የጋራ ግንባር (United Front) በመፍጠር “ሕዝባዊ
ኃይልታት ኤርትራ” ወይም “ሻዕቢያ” የሚለውን ድርጅት አቋቁመው መንቀሳቀስ ጀመሩ፤ ዑስማን ሳልሕ ሳበ
ደግሞ የግንባሩ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ሆኖ እንዲሠራ በመስማማት ጀብሃን ለመቋቋም በአንድነት ተነሱ፡፡
- የእርስ በርሱ ውጊያም እየከረረ በመሄዱ ጀብሃ ከዚህ በፊት በቀላሉ ያስመዘግባቸው የነበሩት ድሎች
ሊገኙ አልቻሉም፡፡ በእርስ በርሱ ውጊያ ውስጥ ሻዕቢያ ምልምል አባሎችን ከደጋው ክፍል በብዛት ያገኝ
ስለነበር፣ እየተጠናከረ መጣ፡፡ ሻዕቢያ በዑስማን ሳልሕ ሳበ እስከ አፍንጫው ድረስ ታጠቀ፡፡ የአንድነቱ ግንባር
ጀብሃን መቋቋም በመቻሉ የጀብሃ አደገኛነት እየመነመነ ስለሄደ ለጊዜው ታፍኖ የነበረው ሁለተኛ ቅራኔ
ማለትም የሥልጣንና የጎሳ ቅራኔ ብቅ ብቅ ይል ጀመር፡፡ ከአንድነት ግንባር ውስጥ በቀይ ባሕር ተወላጆችና
በማሪያ ልጆች (የዑብል አባሎች) መካከል ቅራኔ ስለተፈጠረ በ1966 “ዑበል” ከሻዕቢያ ተገንጥሎ ወደ ባርካ
ሲጓዝ በጀብሃ ተደመሰሰ፡፡ በዚህም የዑበል የእንቅስቃሴ ታሪክ አከተመ፡፡ የተቀሩት የአንድነት ግንባር አባሎች
ማለትም ሕዝባዊ ኃይልና “ሰልፊ ነጻነት” በስምምነት ሂደት ላይ እንዳሉ በ1966 ዓ.ም. የ“መንካዕ” እንቅስቃሴ
ተነሣ፡፡ ይህ የ“መንካዕ” እንቅስቃሴ የአንድነትን ሂደት በማሰናከል በኢሳያስ ቡድን ውስጥ አስጊ ሆኔታን
ፈጠረ፡፡ PDF page 7
View this page in original PDF
7
- “የመንካዕ” እንቅስቃሴ አሥራ አንድ የሚሆኑ ዲሞክራሲ አዘል ጥያቄዎችን የአንድነቱ ግንባር
መሪዎች ለነበሩት ለእነ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ሰለሞን ወ/ማርያም፣ አሥመሮም እንዳ/ጊዮርጊስ፣ መስፍን ሐጎስና
ተወልደ ኢዮብ አቀረበ፡፡ ከጥያቄዎቹም መካከል፤
1- ሰፊው ሕዝብ በመሪዎቹ እንዳይገፋ
2- የብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፕሮግራም አዋጅ እንዲታወጅ
3- የድርጅቱ ጉባኤ ተደርጎ መሪዎቹ በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲመረጡ
4- በድርጅቱ የሰፈነው ወታደራዊ አምባገነንነት እንዲጠፋ
5- ኢሳያስ አፈወርቂ በሞኖፖል የያዛቸውን ኃላፊነቶች እንዲያከፋፍል
6- የፀጥታው ክፍል “በእሥረኞች” ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች የሚፈጽም ስለሆነ፣ ርህራሄ የሰፈነበት ፍርድ
እንዲሰጥ የሚሉ ይገኙበታል፡፡
በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙ አባሎች በሙሉ እንቅስቃሴውን ሲደግፉ ኢሳያስ ግን ባህርዩና ዓላማው
ስለማይፈቅድለት እንቅስቃሴውን ለብቻው ተቃወመው፡፡
የመንካዕ እንቅስቃሴ መሪዎችም፣ የድርጅቱን ሥልጣን ለአሥር ቀናት ያህል ይዘው ኃይላቸውን
ማጠናከር ጀመሩ፡፡ ኢሳያስና ጓደኞቹ መንካዕን ፊት ለፊት በፖለቲካ መመከት ስላልቻሉ አድኃሪ በሆነው
የከፋፍለህ ግዛ ስልት ተጠቅመው ሐማሴን፣ አካለጉዛይ፣ ሠራየ በማለት እርስ በርስ ካነካከሱ በኋላ የተጀመረውን
ንቅናቄ ሊያፍረከርኩት በቁ፡፡ የመንካዕን እንቅስቃሴ በጉልህ ሲመሩ ይታዩ የነበሩት አብዛኞቹ የአካለጉዛይ
ልጆች በመሆናቸው የመንካዕ እንቅስቃሴ በሐማሴንና በአካለጉዛይ ተወላጆች መካከል እንደተነሳ ቅራኔ ሆኖ
ተገመተ፡፡ ሆኖም ያልነቃ ሠራዊት የአድኃሪያን መሣሪያ ከመሆን ስለማያልፍ፣ ብዙዎቹም የሐማሴን ልጆች
ስለነበሩ፣ የኃይል ሚዛን ወደ ኢሳያስና ሰለሞን ወ/ማርያም አዘነበለ፡፡ ከኃላፊነት ወርዶና ተባሮ በየጥላ ሥር
ይውል የነበረው ኢሳያስ አፈወርቂም በሥልጣን ወንበሩ ላይ ተመልሶ ተቀመጠ፡፡ ወዲያውኑ የመንካዕ
እንቅስቃሴ መሪዎች በሙሉ ከታሰሩ በኋላ እንቅስቃሴው የአካለጉዛይ ተወላጆች ብቻ ነው ተብሎ እንዲወራ
ተደረገ፡፡ ከመንካዕ እንቅስቃሴ መሪዎች መካከል ታስረው የነበሩ የሐማሴን ተወላጆች የሆኑት ጴጥሮስ ሰለሞንና
ስብሃት ኤፍሬምም ( አሁን የሻዕቢያ የፖሊት ቢሮ አባሎች) ከእስር ቤት ወጥተው ከሠራዊቱ ፊት ቀርበው
እንቅስቃሴው የአካለጉዛይ ልጆች እንቅስቃሴ መሆኑን ከዋናዎቹ የመንካዕ መሪዎች እንደተገለጸላቸው
በማስመሰል እንዲገልጹ አደረጓቸው፡፡
የተቀሩት የመንካዕ መሪዎች እንደታሰሩ ቀሩ፤ ብዙዎችም ለምሳሌ እንደ ተወልደ፣ ኢዮብ፣ ሙሴ
ተስፋሚካኤል፣ ብጻይ ጎይትኦም፣ ዮሐንስ ስብሃቱና ሌሎችም መሪዎችና ካድሬዎች እንዲገደሉ ተደረገ፡፡ እነ
ኢሳያስ አፈወርቂ ከጥላቻቸው ብዛት የተነሳ ከመንካዕ ቡድን አባሎች የሰበሰብዋቸው ተራማጅ መጽሐፍት፣
በተለይ ጎይትኦም በትግርኛ ተርጉሟቸው የነበሩትን ጽሑፎች፣ ሁሉ አንድም ሳያሰቀሩ አቃጠልዋቸው፡፡
ከዚያ በኋላ በድርጅቱ ውስጥ ፍጹም የሆነ ወታደራዊ አምባገነንነት በመስፈኑ ማንም ተራ አባል
ባለበት ቡድን መንቀሳቀስ፣ መጻፍ፣ ወይም ኃለፊዎችን ማረም የማይችልበት ወጥመድ ውስጥ ገባ፡፡ ማንኛውም
የዚህ ቡድን አመራር ተቃዋሚ በእስር ቤት እንዲማቅቅና በሞት እንዲቀጣ ማድረግ ጀመረ፡፡
“መንካዕ፣ የኢትዮጵያ ሰላይ፣ የሲ.አይ.ኤ. ሰላይ ነው” በሚል ሰበብ ብዙ ዲሞክራቲክ ኤለመንቶችና
ምሁራን ያለፍትሕ ተገደሉ፡፡ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ማቅረብ አስፈሪ በመሆኑ በድርጅቱ ውስጥ መጠራጠርና
ፍርሃት ገነነ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በተራ ወሬና በአሉባልታ አማካይነት የኢሳያስ “ጀግንነት” ይነዛ ነበር፡፡ በዚህ
አንጻር ደግሞ ተቃውሞ ሊያቀርብ የሚችለውን ምሁር ከተቀሩት የገበሬና የሠራተኛው ክፍል ጋር በማጣላት
ሠራዊቱ ተከፋፍሎና እርስ በርስ ተፈራርቶ እንዲኖር ስለተደረገ የኢሳያስ ገናናነት ብቅ ይል ጀመር፡፡
በሥልጣን ሊወዳደረው የሚችል በብዙ መንገድ ስለጠፋ በርሱና በተከታዮቹ ማለትም በሌሎች መሪዎች መካከል
ያለው የሥልጣን ልዩነት ሰማይና መሬት ሆነ፡፡ እስከ 1969 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የቀድሞዎቹ መሪዎች
በሙሉ የእርስ በርስ ድክመታቸውን ስለሚተዋወቁ ለኢሳያስ የሚታዘዙ አልነበሩም፡፡ እነዚህን ሁሉ አስወግዶ
ብዙ ደካማ ጎን ያላቸውን መሪዎች ሥልጣን ማስጨበጡ ኢሳያስ ላለው አምባገነናዊ አመራር አመቺ ሆኔታን
ለመፍጠርና ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የመጀመሪያ ጉባኤ በ1970 ዓ.ም. እንዲካሄድ ተወሰነ፡፡
በ1970 ዓ.ም. የድርጅቱ የመጀመሪያ ጉባኤ ተደረገ፡፡ ጉባኤው ያለምንም ተቃውሞ እንዲከናወን
ስለተፈለገ ተቃውሞ ሊኖር እንደማይችል ተደርጎ ተዘጋጀ፡፡ ጉባኤው እና ድርጅቱም ኢሳያስ በፈለገው ዓይነት
ተዋቀረ፡፡ በዚሁ መሠረት የድርጅቱ ሥልጣን በሙሉ ምክትል ዋና ፀሐፊ ሆኖ ለተመረጠው ለኢሳያስ
እንዲሰጠው ተደረገ፡፡ በዚሁ ጉባኤ ላይ የተቋቋመው ማዕከላዊ ኮሚቴ 37 አባሎችን ይይዛል፡፡ ኢሳያስ ተንኮሉን
አይተውምና ለራሱ ዓላማ እንዲያመቸው ከ37ቱ አባሎች መሐል አስራ ዘጠኙ ደገኞች ሲሆኑ፤ አስራ ስምንቱ PDF page 8
View this page in original PDF
8
ደግሞ የቀይ ባሕር ተወላጆች እንዲሆኑ አደረገ፡፡ በመሆኑም ኢሳያስ በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ከፍተኛ ድምጽ
አለው ማለት ነው፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴ በሌለበት ጊዜ ሥራውን የሚያካሄዱ 13 አባሎች ያሉት ፖሊት ቢሮ
ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባሎች መሐል ተመርጠው ተቋቁሟል፡፡ ከነዚህም ሰባቱ ደገኞች ሲሆኑ፣ ስድስቱ ደግሞ የቀይ
ባሕር ተወላጆች ናቸው፡፡
የማዕከላዊ ኮሚቴ አባሎች የተመረጡት ችሎታ ኖሯቸው ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደም ደካማ ጎን ስላላቸው
ታዛዥ ሆነው እንዲያገለግሉ ሆን ተብሎ በኢሳያስ የተመረጡ ቡችሎቹ ናቸው፡፡
ለምሳሌ፤
1. ተክለ ዓንዶም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የብርጌድ 76 የፖለቲካ ኮሚሳር በ1962 ዓ.ም. ከጀብሃ
በማምለጥ ለኢትዮጵያ መንግሥት እጁን ሰጠ፡፡ በ1964 ዓ.ም. ደግሞ የኢሳያስ ቡድን ከተቀላቀለ በኋላ ተመልሶ
ለመንግሥት እጁን ሰጠ፡፡ እንደገናም በ1966 ዓ.ም. ወደ ሻዕቢያ ተመልሶ በመግባት የመገንጠል እንቅስቃሴውን
እስከአሁን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ሰው ይህንን የመሰለ ድርጊት ፈጽሞ ኢሳያስን መቃወም አይችልም፡፡
2. እስጢፋኖስ ሥዩምና፣ ዓንደጊዮርጊስ የኢኮኖሚና የሬድዮ ክፍል ኃላፊዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም በ1969
ዓ.ም. ሻዕቢያን የተቀላቀሉ እና ለጉባኤው አዲስ በመሆናቸው ማን ምን እንደሆነ ለመናገር የማይችሉ ዱዳዎች
ናቸው፡፡
3. ኤፍሬም ስብሓትና ጴጥሮስ ሰለሞን አሁን የፖሊት ቢሮ አባሎች ቀደም ሲል በ1966 ዓ.ም. በመንካዕ
ንቅናቄ ውስጥ የተሣተፉ ከፍተኛ የሆነ የክሕደት ተግባር የፈጸሙ ግለሰቦች ስለሆኑ፣ በኢሳያስ ላይ ለመነሳት
የማይችሉ ደካሞች ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ሆኔታ ሌሎችም በዛ ያሉ የማዕከላዊ ኮሚቴው አባሎች በኢሳያስ
ጉዳቸው የሚታወቅባቸው ስለሆነ፣ መሣሪያዎች እንዲሆኑ ኢሳያስ መርጥዋቸዋል፡፡
- በአሁኑ ጊዜ የሻዕቢያ መሪዎች ከፍተኛ በሆነ የፖለቲካና የወታደራዊ ውጥረት ላይ ይገኛሉ፡፡
ተገንጣዮቹ በተለመደ የማወናበጃ ዘዴያቸው ተስፈንጣሪ መሰል መፈክሮቻውን ከማነብነብ በስተቀር ጭልጥ
ብለው ቀድሞ ከመሠረቷቸው ኢምፔሪያሊስቶች ጉያ ተወሽቀዋል፡፡ የሻዕቢያ መሪዎች በተለይ ተለዋዋጭ
ታክቲኮችን በመቀየስ በየቀኑ አቋማቸውን ይለዋውጣሉ፡፡ “ ታክቲክና እስትራቴጂ” ሳይንሳዊ ትርጉምና
ዲያሌክታዊ አንድነት ያላቸው ጽንሰ ሐሳቦች ሲሆኑ፣ የሻዕቢያ መሪዎች ግን በተለይ ታክቲክን እንደ ላስቲክ
እንደፈለጉትና እንዳሻቸው ሲስቡትና ሲጠመዝዙት ቆይተዋል፡፡ ከዑስማን ሳልሕ ሳበ ጋር ከ1965 እስከ 1968
ዓ.ም. የነበረው ግንኙነት ከአድሃሪ ጋር የሚደረግ ልዩ ታክቲክ ነው በማለት ሳያመነቱ አወሩ፡፡ በ1974 ዓ.ም.
ደግሞ በሳውዲ ኢሳያስ በሰጠው ቃለ መጠየቅ “እኔም ሆንኩኝ ድርጅቱ ማርክሲስቶች አይደለንም” በማለት
የሰጠው መልስ የሳውዲን መንግሥት ለማስደሰት የተደረገ ታክቲክ ነው ተባለ፡፡ የአሁኑ አዲስ ታክቲክ ደግሞ
ከኢራቅ የባዓስ ፓርቲ ጋር ግንኙነት በመፍጠር በኤርትራ ካሉት ተገንጣይ ቡድኖች አንዱ ከሆነውና በዑስማን
ዓጀብ ከሚመራው ድርጅት መካከል የባዓስ ፓርቲ ተከታይ “ከሕዝባዊ ኃይልታት ሐርነት ማዕከላይ ባይቶ”
አንድነት መፍጠር ነው ሲል አቋሙን እንደእስስት ይለዋውጣል፡፡ ለመሆኑ በአፍሪቃ ቀንድ ኢምፔሪያሊዝም
ማረፊያ እንደአጣች አውሮፕላን ተጨንቆ ሲባዝን ተገንጣይ ቡድኖች ማረፊያ ሜዳ ለመስጠት
የሚፍጨረጨሩበት ምክንያት ምን ይሆን? ይህ በቀጥታ የኢምፐሪያሊዝም አሻንጉሊት መሆናቸውን
አያስረዳንም? የታክቲክስ ትርጉም ይህን ያህል ሊዛባ ይችላል?
-እንግዲያውስ ታክቲክ ይህን ከመሰለ ተገንጣዮቹ ነገ ከእስራኤልና ከደቡብ አፍሪካ ጋር የሚፈጥሩትን
ግኑኝነት ሕጋዊ አይሉት ይሆን?
-የሻዕቢያ ጉድ ሀ እና ፐ ተብሎ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ጊዜው ይርዘም ይጠር እንጂ
ዕውነት እውነትነቷን ሳታረጋግጥ ተድበስብሳ ትቀራለች ማለት ዘበት ነውና የተገንጣዮች ፀረ ሕዝብነት ራቁቱን
ቀርቷል፡፡
-በታሪክ ሠሪው ሰፊ ሕዝብ ላይ፣ አድኃሪያን የፈለጉትን ያህል ሴራ ቢጠነስሱበትና በአብዮቱም ላይ
ቢረባረቡበት፣ በመጨረሻ እነዚህን ስግብግብ ግለሰቦችና ፀረ ሕዝቦች ደቁሶ በድል እንደሚወጣ አያጠራጥርም፡፡
*******************